ስለ እኛ
መግቢያ
ይህ አጭር ጽሑፍ የ “አዎንታዊ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ ማሕበር (አአኢማ)” በማህበሩ ውስጥ አባል ለሆኑ እና አባል ለመሆን ለሚፈልጉ ሁሉ የ “አዎንታዊ አስተሳሰብ” ፅንሰ ሀሳብ መገለጫዎቹን እና ጥቅል ትርጓሜን፣ ማሕበሩ በተጨባጭ በዜጎች አብሮ የመኖር ይዘትና ሂደት ውስጥ የሚከተላቸውን መርሆዎችና ዕሴቶችን ይዟል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ “አዎንታዊ አስተሳሰብ” ለአአኢማ አባለት የባህሪ እና የአባልነት መገለጫ ስለመሆኑ በአመላካች ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ይዟል፡፡
ጠቅለል ባለ ዕሣቤ “አዎንታዊ አስተሳሰብ” ማለት ነገሮችን በቀና መንፈስ ማየት ነው፡፡ ከግለሰብ እስከ ሀገር ጉዳይ የሚፈጠሩ የሃሣብ ልዩነቶችን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ያለአድልዎ ሁሉንም ሰው ሊያስማማ በሚችል መልኩ በውይይትና በምክክር መፍትሔ ማስገኘት የአዎንታዊ አስተሳሰብ ውጤት ነው፡፡ ይህ ታሪክና ትርክቶችን በአዎንታዊ አስተሳሰብ በመዳሰስና በመቀበል ለሀገር ሰላም፣ አንድነትና ለህብረተሰቡ ብልጽግና የማዋል አሴት ማድረግን ያካትታል፡፡ በተለይ በሀገራዊ ሀብት ክፍፍልና አጠቃቀም ዙሪያ ኢትዮጵያ ለሁሉም የሚበቃ በቂ ሀብት አላት፡፡ ስለዚህ ይህን ሀብት በፍትሃዊነት በጋራ መጠቀም ይቻላል የሚልን በጐ አስተሳሰብ የሚያበረታታ ነው፡፡
‘የሀገርን ሀብት እኔ ብቻ ልውሰድ’ የሚል ስግብግብነት፣ በዚህ ዕሳቤም ሕዝብን ለድህነትና ለኋላቀርነት የዳረጉ፣ በራስ ያለመተማመን ውጤት የሆኑት የከፋ ጥርጣሬ፣ የጓደኛ ስኬትን እንደ እራሳቸው ውድቀት የሚያስቡ በመመቀኘት መቸገርን የመሳሰሉትን ንፉግ አስተሳሰቦች ለመቀየርና ግላዊ ጤንነትን ለመጐናጸፍ አዎንታዊ አሰተሳሰብ አስተተዋፅኦው ከፍተኛ ነው፡:
የአዎንታዊ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ ማህበር ራዕይ ፣ ተልዕኮና እሴቶች
ራዕይ
በአዎንታዊ አስተሳሰብ መርሆዎች ሁለንተሃዊ ሀገራዊ ችግሮች እየተፈቱ ፍትሃዊነት፣ አብሮነት፣ ሰላምና ብለፅግና በኢትዮጵየ ሰፍኖ ማየት
ተልዕኮ
በአዎንታዊ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ላይ በመሥራት ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን ለሀገር ዕድገት የሚተጋ ትውልድን በመቅረጽ የባህል ለውጥ ተመዝግቦ የድህነትና የኃላቀርነት ታሪክን በመፋቅ ሂደት የበኩልን አሻራ ማኖር፡፡
መነሻ ጭብጦች እና ታሪካዊ ዳራ
የኢትዮጵያ ታሪክ ከውስጥ በሚፈጠሩና ከውጭ በሚመጡ ግጭቶችና ጦርነቶች የተሞላ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ዛሬም ቀጥሏል፡፡ ሰላም ሰፍኖ አገሪቷ ልማት ላይ አትኩራ የኤኮኖሚና የማኅበራዊ ዕድገት ያገኘችባቸው ጊዜያት በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ለምን ወደኋላ ቀረን? ቢባል አንዱ ምክንያትም ይህ ነው፡፡ በሌላም በኩል የምቀኝነት፣ የመገዳደልና የመጠፋፋት ባሕልም በሰፊው ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ወንድሙ ወይም ጎረቤቱ ሰርቶ፣ ለፍቶ፣ ሲሻሻል መንፈሳዊ ቅናት አድሮበት እኔም እንደርሱ ሰርቼ፣ ለፍቼ፣ ራሴን ላሻሽል፤ በማለት ፈንታ ለምን በለጠኝ? ብሎ ወንድሙን ወይም ጎረቤቱን እንዴት እንደሚያሰናክለው፣ ወይም ከነጭራሹ እንዴት እንደሚያጠፋው የሚያስብ ሰው በጣም በርካታ ነው፡፡ በጎ በማድረግና ሌሎችን በመርዳት ትልቁን ደስታ፣ የመንፈስ እርካታን፣ ለማግኘት ከመጣር ይልቅ ሥራቸው ተንኮል ማሰብና ሌላውን ማሰናከል የሆኑ ሰዎች በየቦታው፣ በየቢሮው ሞልተዋል፡፡ በአጭሩ በአገራችን ውስጥ የአዎንታዊ አስተሳሰብ ጉድለት ያለባቸው ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
በዚህ አሉታዊ አስተሳሰብ ፈንታ የበጎነት፣ የቅንነት፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ አዎንታዊ አስተሳሰብ ቢዳብር አገር ሰላም ታገኛለች፣ መንግሥትና ሕዝብ ይረጋጋል፣ ልማት ይፋጠናል፣ አንድነት በእኩልነት ይዳብራል፡፡ “በጎ ተመኙ፣ በጎ እንድታገኙ፤” የሚለውን ብሂልና የሁሉም ሃይማኖቶች አስተምሕሮ የሆነውን “በአንተ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገውን በሌሎች ላይ አታድርግ፤” የሚለውን ትዕዛዝ ሁሉም በተግባር ቢፈጽም አገራችንና ዓለማችን ምንኛ መልካም ትሆን እንደነበር አዎንታዊ አስተሳሰብን ለጤነኛ ሕይወትና ኑሮ እንደ ግብዓት የሚጠቀሙ ሰዎች ይገነዘባሉ፡፡
ቀዳሚ መርሆዎችና ዕሴቶች
አአኢማ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የበርካቶች ድሀ መሆን፣ መራብ፣ መታረዝና መጎሳቆል፣ በአጠቃላይ የሀገሪቷ ሕዝቦች የኑሮ ደረጃ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘት በሀገሪቷ ውስጥ አዎንታዊ አስተሳሰብ ያላቸው ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ከሄደ ሊሻሻል እንደሚችል ያምናል፡፡ የአአኢማ መሠረታዊ ዓላማና ተግባር ይህን ሀገርና ሰውን ገንቢ የሆነውን የቀናነትና የበጎነት አስተሳሰብ በሕብረተሰቡና በወሳኝ ተቋማት የአመራር አካላት ውስጥ በማስረጽ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ችግሮቻችን መፍትሔ እንዲያገኙ መጣር ነው፡፡ ለዚህም ሳያሰልስ ህብረተሰቡን ለማስተማርና ለማንቃት ይሠራል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ሥራ ደግሞ ዋነኛ መርሆዎቹና ዕሴቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡:
የመደማመጥ፣ እራስን በሌላው ጫማ ውስጥ በማስቀመጥና እርስ በርስ በመረዳዳት፣ ክብርና ኃላፊነት በመሰጣጣት፣ በመተሳሰብና ጥምረትን በመፍጠር ለግልና ለጋራ ጥቅም መሥራትን የዘወትር ተግባር ማድረግ፤
ግብረገብ፣ ሞራል እና ሥነ ምግባር አዎንታዊ በሆነ መንፈሳዊና ሰብአዊ ይዘቱ በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲስፍን እና እንዲጎለብት ማድረግ፤ ፅዩፍ እና እኩይ የሆኑ እንደ ሌብነት፣ ሙሰኝነት፣ ያለአግባብ ተጠቃሚነት፣ ምቀኝነት፣ አግላይነት ዕሳቤዎችና ተግባራትን አበክሮ መታገል፣ ስኬትና ስኬታማ ዜጐችን ማድነቅ፣ ዕውቅና መስጠት፤
እራስን በትምህርት፣ በማንበብ፣ በሥልጠና በማበልጸግ እንዲሁም ከአዋቂዎች ልምድ በመገብየት ከሌሎች ጥገኝነት እና አካባቢያዊ ተፅዕኖዎች በመላቀቅ ውሳኔዎችን በምክንያታዊነት በራስ መወሰን መቻል፡፡ እንዲሁም የፈጠራ ሥራዎችን በማስፋፋት ምርታማነት እና ትርፋማነት በየዘርፉ እንዲጨምር አስተዋጽኦ ማድረግ፡፡
የሕዝብ አስተዳደርና ፖለቲካዊ ሥርዓቱ ማናቸውንም ሰው በእኩልነት የሚያይ፣ የሕግ የበላይነት የሚከበርበትና የአስተዳደርና የፖለቲካ ሥርዓት ቀረጻና ግንባታ አካታችና አሳታፊ መሆን እንደአለበት ማስተማር፣ ማስገንዘብ፣ የአስተዳደርና የፖለቲካ ችግርና ተግዳሮት ግልጽነትን ማስፈን፤ ልዩነቶች በውይይትና በምክክር መድረክና ሥርዓት ሊፈቱ እንደሚችሉ ማሳወቅ፣ ለተግባራዊነቱም አበክሮ መሥራት፤
ቀዳሚ መርሆዎችና ዕሴቶች
የእኔ ሃሣብ ብቻ ትክክል ነው” ብሎ ከማማን የራስ ወዳድነት/በላይነት (ኢጐ) ከመጠቃት ግትር፣ ትዕቢተኝነት፣ ጀብደኝነት፣ ከመሳሰሉት እኩይ ተግባራት እራስን ለማፅዳት መሥራት፣ የሚነሱ ሃሣቦችን በማሳመን፣ ወይም በማመን ይህ የማይቻል ከሆነ ጊዜው እስከሚፈታ ድረስ ላለመስማማት በማስማማት እንጂ አንጃ በመፍጠር ወይም እራስን ከስብስቡ ማግለል ነውር እና የብስለት ችግር መሆኑን መረዳት፣ ማስረዳት፤
በማናቸውም ዐውድ ውስጥ የሚከሰት ችግር ሆነ ተግዳሮት በግጭት፣ በተለይም በጦር መሣሪያ በሚከወን ትግል ሳይሆን በውይይት፣ በመነጋገር፣ በመመካከር፣ በድርድር ብቻ መፍትሔ ሊያገኝ እንደሚችል ማስገንዘብ፣ ለመፍትሔውም ሳይሰለቹ መሥራት፤
ሙስናን፣ አድሎአዊነትንና የሴቶችን መብት መጣስን መጸየፍና ለዚህ ተጠያቂ የሆኑትን ማጋለጥ፤ በሕዝብ እስከ መገለል የሚያደርስ ማህበረሰባዊ ቅጣት እንዲፈጸምባቸው የማድረግ ትግል ማካሄድ፤
8. ዜጎች በማናቸውም ዐውድ ውስጥ ያላቸውን ሀብት፣ ዕውቀትና የሥራ ልምድ ይዘው በየትኛውም የሀገሪቷ ክፍል ውስጥ በነፃነት ሊንቀሳቀሱና ሊሠሩ እንደሚችሉ፣ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ዜጎች በማንነታቸው ላይ የተመሠረተ የምቀኝነት፣ የተንኮልና ሴራ እኩይ ድርጊት ሰለባ እንዳይሆኑ ማስገንዘብ፤
የአባለት ተጠባቂ ባህሪያትና መገለጫዎች
አአኢማ ከላይ የቀረቡት መርሆዎችና ዕሴቶች በሀገሪቷ ውስጥ ለሚቀረፁና ለሚተገበሩ የፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ፕሮግራም እና ኢንስቲትዩት (ፖስፕኢ) ውጤታማነት አስተዋፆአቸው የጎላ ነው ብሎ ያምናል፡፡
አባላቱም በነዚህ መርሆዎችና ዕሴቶች በመመራት በሀገሪቷ የተለያዩ ዐውዶች ውስጥ በሚደረጉ የፖስፕኢ ቀረፃና ትግበራ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይጠበቃል፡፡
ለማህበሩ አባልነት የሚታጭ እና ብሎም አባል የሚሆን ማናቸውም ሰው ምንም ዓይነት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ይዘት ይኑረው/ይኑራት፣ በየትኛውም ዘር፣ ጎሳ፣ ብሔር፣ ቆዳ ቀለም፣ ቋንቋ እና ሃይማኖት ወዘተ ማዕቀፍ ውስጥ ይገኝ፣ ከላይ ለተዘረዘሩት መርሆችና ዕሴቶች ተገዢ ከሆነ ብቻ ነው ለአባልነት እጩ መሆን የሚችለው፡፡ አባል ከሆኑም በኁላ እነዚህን መርሆዎችና ዕሳቤዎች ከ‹‹አዎንታዊ አስተሳሰብ›› ፅንሰ ሀሳባዊ መገለጫዎች ጋር በማጎዳኘት የሚያራምዱ እና የሚተገበሩ እንዲሆኑም ይጠበቃል፡፡ እነዚህ ባህሪያት ዘርዘር ተደርገው ሲታዩይ የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-
የአአኢማ አባላት ዜጎች በሕዝብ እና ሀገር አስተዳደር፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች እና የሚሰጧቸውን አስተያየቶች በሰውነታቸው እንጂ ከብሔር፣ ከቋንቋ፣ ከሃይማኖት ወዘተ ማንነታቸው ጋር አጋምደው አያዩም፤
ለማዳመጥ ዝግጁ የሆኑ፣ የራሳቸውን ሀሳብ በግልፅነት፣ ቅንነትና በበጎ አመለካከት ለማቅረብና ለማስረዳት የሚጥሩ፣ ሌሎችን ተገቢ ባልሆነ መንገድ የማይጎነትሉ፣ ወደ አልተገባ ግጭትና ጥላቻም የማይመሩ፤
አባላቱ ማናቸውም ሰው የሚያነሳውን ሀሳብ በበጎ፣ በቅን ምልከታና ዕሳቤ ቅቡልነት ሰጥተው ለውይይትና ምክክር የሚያቀርቡ፣ የሚያስተናገዱና ራሳቸውንም ተሳታፊ የሚያደርጉ መሆናቸው፤
አባላት ከሙሰኝነት፣ ከሌብነት፣ ከእራስ ብቻ ወዳድነት፣ አድርባይነት ወይም አጐባዳጅነት ከመሳሰሉት እኩይ ተግባራት የተጠበቁና በራሳቸው የሚተማመኑ መሆን፤
የፖለቲካ ፅንፈኝነትን የማይቀበሉ፣ ለውይይት፣ ምክክር፣ ሽምግልና ተገዚ የሆኑ ሥርኣቶችን የሚከተሉ የሆኑ፤
አባላቱ በሚሠሯቸው ሥራዎችና በሚያደርጓቸው እንቀስቃሴዎች ሁሉ ለሕግ ተገዢ ሆነው ሕጋዊ በሆነ መንገድ ማናቸውም ሰው እና ተቋም የሚጠይቁ፣ ተጠያቂ እንዲሆንም የሚያመቻቹ ናቸው፡፡
አባላቱ በአዎንታዊ አስተሳሰብ መጠመድ እርካታና ደስተኝነትን በማጐናጸፍ የሥነ ልቦና ጤንነትን ያስገኛል ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡
በደስታና በፈገግታ ወቅት ሰውነት ለጤንነት አስፈላጊ የሆኑ ሆርሞኖችን በማመንጨት ከልብ ሕመም ከመሳሰሉት በሽታዎች ይታደጋል፤ ብሎም ረዥም ዕድሜ ለመኖርም የሚጠቅም ነው ብለው በማመን ዜጐች አዎንታዊ ሃሣቢ እንዲሆኑ ጥረት የሚያደርጉ፣ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን የሚመክሩ ናቸው ፡፡
በአጠቃላይ የአአኢማ አባለት በሕዝብ አስተዳደርና በፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ የሚነሱ ችግሮችን እና ተግዳሮቶችን የሚረዱት እና የሚቀበሏቸው በአዎንታዊ አስተሳሰብ፣ በውይይት፣ በመነጋገርና በሰጥቶ መቀበል ወይም በጋራ አሸናፊነት ሊፈቱ እንደሚችሉ በማማን ነው፡፡ ይህን ለመተግበርም ዝግጁና ብቁ ሆነው ለመገኘት ተግተው ያጠናሉ፣ ከሙያተኞች እና አዋቂዎችም ለመማር እና ጥበብን ለመሸመት ይጥራሉ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ቅቡልነት ያላቸውን ባህላዊ፣ ማህበራዊ፣ እንዲሁም የእምነት ሥርዓቶችና አደረጃጀቶችን ለመጠቀም መቻልና ብቁ ሆኖ መገኘት ይጠበቅባቸዋል፡:
መነሻ ጭብጦች እና ታሪካዊ ዳራ
የኢትዮጵያ ታሪክ ከውስጥ በሚፈጠሩና ከውጭ በሚመጡ ግጭቶችና ጦርነቶች የተሞላ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ዛሬም ቀጥሏል፡፡ ሰላም ሰፍኖ አገሪቷ ልማት ላይ አትኩራ የኤኮኖሚና የማኅበራዊ ዕድገት ያገኘችባቸው ጊዜያት በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ለምን ወደኋላ ቀረን? ቢባል አንዱ ምክንያትም ይህ ነው፡፡ በሌላም በኩል የምቀኝነት፣ የመገዳደልና የመጠፋፋት ባሕልም በሰፊው ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ወንድሙ ወይም ጎረቤቱ ሰርቶ፣ ለፍቶ፣ ሲሻሻል መንፈሳዊ ቅናት አድሮበት እኔም እንደርሱ ሰርቼ፣ ለፍቼ፣ ራሴን ላሻሽል፤ በማለት ፈንታ ለምን በለጠኝ? ብሎ ወንድሙን ወይም ጎረቤቱን እንዴት እንደሚያሰናክለው፣ ወይም ከነጭራሹ እንዴት እንደሚያጠፋው የሚያስብ ሰው በጣም በርካታ ነው፡፡ በጎ በማድረግና ሌሎችን በመርዳት ትልቁን ደስታ፣ የመንፈስ እርካታን፣ ለማግኘት ከመጣር ይልቅ ሥራቸው ተንኮል ማሰብና ሌላውን ማሰናከል የሆኑ ሰዎች በየቦታው፣ በየቢሮው ሞልተዋል፡፡ በአጭሩ በአገራችን ውስጥ የአዎንታዊ አስተሳሰብ ጉድለት ያለባቸው ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
በዚህ አሉታዊ አስተሳሰብ ፈንታ የበጎነት፣ የቅንነት፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ አዎንታዊ አስተሳሰብ ቢዳብር አገር ሰላም ታገኛለች፣ መንግሥትና ሕዝብ ይረጋጋል፣ ልማት ይፋጠናል፣ አንድነት በእኩልነት ይዳብራል፡፡ “በጎ ተመኙ፣ በጎ እንድታገኙ፤” የሚለውን ብሂልና የሁሉም ሃይማኖቶች አስተምሕሮ የሆነውን “በአንተ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገውን በሌሎች ላይ አታድርግ፤” የሚለውን ትዕዛዝ ሁሉም በተግባር ቢፈጽም አገራችንና ዓለማችን ምንኛ መልካም ትሆን እንደነበር አዎንታዊ አስተሳሰብን ለጤነኛ ሕይወትና ኑሮ እንደ ግብዓት የሚጠቀሙ ሰዎች ይገነዘባሉ፡፡