ልዩ የሚያደርገን ምንድን ነው?
የ“አዎንታዊ አስተሳሰብ” ፅንሰ-ሐሳብ መገለጫዎች
ይህ አጭር ጽሑፍ የ “አዎንታዊ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ ማሕበር (አአኢማ)” በማህበሩ ውስጥ አባል ለሆኑ እና አባል ለመሆን ለሚፈልጉ ሁሉ የ “አዎንታዊ አስተሳሰብ” ፅንሰ ሀሳብ መገለጫዎቹን እና ጥቅል ትርጓሜን፣ ማሕበሩ በተጨባጭ በዜጎች አብሮ የመኖር ይዘትና ሂደት ውስጥ የሚከተላቸውን መርሆዎችና ዕሴቶችን ይዟል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ “አዎንታዊ አስተሳሰብ” ለአአኢማ አባለት የባህሪ እና የአባልነት መገለጫ ስለመሆኑ በአመላካች ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ይዟል፡፡
ጠቅለል ባለ ዕሣቤ “አዎንታዊ አስተሳሰብ” ማለት ነገሮችን በቀና መንፈስ ማየት ነው፡፡ ከግለሰብ እስከ ሀገር ጉዳይ የሚፈጠሩ የሃሣብ ልዩነቶችን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ያለአድልዎ ሁሉንም ሰው ሊያስማማ በሚችል መልኩ በውይይትና በምክክር መፍትሔ ማስገኘት የአዎንታዊ አስተሳሰብ ውጤት ነው፡፡ ይህ ታሪክና ትርክቶችን በአዎንታዊ አስተሳሰብ በመዳሰስና በመቀበል ለሀገር ሰላም፣ አንድነትና ለህብረተሰቡ ብልጽግና የማዋል አሴት ማድረግን ያካትታል፡፡
በተለይ በሀገራዊ ሀብት ክፍፍልና አጠቃቀም ዙሪያ ኢትዮጵያ ለሁሉም የሚበቃ በቂ ሀብት አላት፡፡ ስለዚህ ይህን ሀብት በፍትሃዊነት በጋራ መጠቀም ይቻላል የሚልን በጐ አስተሳሰብ የሚያበረታታ ነው፡፡ ‘የሀገርን ሀብት እኔ ብቻ ልውሰድ’ የሚል ስግብግብነት፣ በዚህ ዕሳቤም ሕዝብን ለድህነትና ለኋላቀርነት የዳረጉ፣ በራስ ያለመተማመን ውጤት የሆኑት የከፋ ጥርጣሬ፣ የጓደኛ ስኬትን እንደ እራሳቸው ውድቀት የሚያስቡ በመመቀኘት መቸገርን የመሳሰሉትን ንፉግ አስተሳሰቦች ለመቀየርና ግላዊ ጤንነትን ለመጐናጸፍ አዎንታዊ አሰተሳሰብ አስተተዋፅኦው ከፍተኛ ነው፡፡
የአዎንታዊ አስተሳሳብ በተለያዩ ዐውዶች እለታዊ እንቀስቃሴ ውስጥ ማስረፅ ደግሞ የዚህ ዓይነቱ ፈተናን በብርታትና በበጎ አሸነፊነት ለመሻገር ብሎም ለበርካታ ኢትዮጵውያን ከድህነት አረንቋ፣ ከረሃብ፣ እርዛት እና ጉስቁልና እንዲላቀቁ ለማድረግ ሕሊናዊ፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ መሠረት ያስገኛል፡፡
አአኢማ በአንድ ሕብረተሰብና ሀገር ውስጥ የዜጎች ዐውዳዊ እንቀስቃሴ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካና ሃይማኖታዊ ክፍፍል ተለይቶ ሊጠና፣ ሊመረመር፣ ሊገመገም እና ማብራሪያ ሊቀርብበት እንደሚቻል ይገነዘባል፡፡
በነዚህ ዐውዳዊ ክፍፍሎች ላይ ተመሥርቶ ከማህበሩ የፖሊሲ አቋሞች አንዱ ዛሬ ላይ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት፣ ልማትና ብልፅግና ሥራዎች ዋነኛ ግብዓት ናቸው ተብለው ሊጠቀሱ ከሚችሉት መሃል ቀዳሚ መሆን ያለበት የዜጎች “በአዎንታዊ አስተሳሳብ” መታነጽ ነው የሚል ነው፡፡
አዎንታዊ አስተሳሰብ ዜጎች በሁሉም ዐውዶች ውስጥ በሚያደርጓቸው ግንኙነቶችና መስተጋብሮች ውስጥ ለአዎንታዊ፣ ቀልጣፋና ብቁ ውጤት፣ ለሚመዘን እና በዕውን ለሚታይ የዜጎች ኑሮ መሻሻል አስተዋፅኦው የጎላ ነው የሚል መሠረትም ይዟል፡፡ በመሆኑም “አዎንታዊ አስተሳሳብ” እንደ የአገር ግንባታ ግብዓት ሚናው ከፍ ያለ ነው፡፡
መነሻ ጭብጦች እና ታሪካዊ ዳራ
የኢትዮጵያ ታሪክ...
የኢትዮጵያ ታሪክ ከውስጥ በሚፈጠሩና ከውጭ በሚመጡ ግጭቶችና ጦርነቶች የተሞላ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ዛሬም ቀጥሏል፡፡ ሰላም ሰፍኖ አገሪቷ ልማት ላይ አትኩራ የኤኮኖሚና የማኅበራዊ ዕድገት ያገኘችባቸው ጊዜያት በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ለምን ወደኋላ ቀረን? ቢባል አንዱ ምክንያትም ይህ ነው፡፡ በሌላም በኩል የምቀኝነት፣ የመገዳደልና የመጠፋፋት ባሕልም በሰፊው ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ...
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ወንድሙ ወይም ጎረቤቱ ሰርቶ፣ ለፍቶ፣ ሲሻሻል መንፈሳዊ ቅናት አድሮበት እኔም እንደርሱ ሰርቼ፣ ለፍቼ፣ ራሴን ላሻሽል፤ በማለት ፈንታ ለምን በለጠኝ? ብሎ ወንድሙን ወይም ጎረቤቱን እንዴት እንደሚያሰናክለው፣ ወይም ከነጭራሹ እንዴት እንደሚያጠፋው የሚያስብ ሰው በጣም በርካታ ነው፡፡ በጎ በማድረግና ሌሎችን በመርዳት ትልቁን ደስታ፣ የመንፈስ እርካታን፣ ለማግኘት ከመጣር ይልቅ ሥራቸው ተንኮል ማሰብና ሌላውን ማሰናከል የሆኑ ሰዎች በየቦታው፣ በየቢሮው ሞልተዋል፡፡ በአጭሩ በአገራችን ውስጥ የአዎንታዊ አስተሳሰብ ጉድለት ያለባቸው ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
በዚህ አሉታዊ ....
በዚህ አሉታዊ አስተሳሰብ ፈንታ የበጎነት፣ የቅንነት፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ አዎንታዊ አስተሳሰብ ቢዳብር አገር ሰላም ታገኛለች፣ መንግሥትና ሕዝብ ይረጋጋል፣ ልማት ይፋጠናል፣ አንድነት በእኩልነት ይዳብራል፡፡ “በጎ ተመኙ፣ በጎ እንድታገኙ፤” የሚለውን ብሂልና የሁሉም ሃይማኖቶች አስተምሕሮ የሆነውን “በአንተ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገውን በሌሎች ላይ አታድርግ፤” የሚለውን ትዕዛዝ ሁሉም በተግባር ቢፈጽም አገራችንና ዓለማችን ምንኛ መልካም ትሆን እንደነበር አዎንታዊ አስተሳሰብን ለጤነኛ ሕይወትና ኑሮ እንደ ግብዓት የሚጠቀሙ ሰዎች ይገነዘባሉ፡፡
ቀዳሚ መርሆዎችና ዕሴቶች
አአኢማ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የበርካቶች ድሀ መሆን፣ መራብ፣ መታረዝና መጎሳቆል፣ በአጠቃላይ የሀገሪቷ ሕዝቦች የኑሮ ደረጃ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘት በሀገሪቷ ውስጥ አዎንታዊ አስተሳሰብ ያላቸው ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ከሄደ ሊሻሻል እንደሚችል ያምናል፡፡ የአአኢማ መሠረታዊ ዓላማና ተግባር ይህን ሀገርና ሰውን ገንቢ የሆነውን የቀናነትና የበጎነት አስተሳሰብ በሕብረተሰቡና በወሳኝ ተቋማት የአመራር አካላት ውስጥ በማስረጽ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ችግሮቻችን መፍትሔ እንዲያገኙ መጣር ነው፡፡ ለዚህም ሳያሰልስ ህብረተሰቡን ለማስተማርና ለማንቃት ይሠራል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ሥራ ደግሞ ዋነኛ መርሆዎቹና ዕሴቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡:
የመደማመጥ፣ እራስን በሌላው ጫማ ውስጥ በማስቀመጥና እርስ በርስ በመረዳዳት፣ ክብርና ኃላፊነት በመሰጣጣት፣ በመተሳሰብና ጥምረትን በመፍጠር ለግልና ለጋራ ጥቅም መሥራትን የዘወትር ተግባር ማድረግ፤
ግብረገብ፣ ሞራል እና ሥነ ምግባር አዎንታዊ በሆነ መንፈሳዊና ሰብአዊ ይዘቱ በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲስፍን እና እንዲጎለብት ማድረግ፤ ፅዩፍ እና እኩይ የሆኑ እንደ ሌብነት፣ ሙሰኝነት፣ ያለአግባብ ተጠቃሚነት፣ ምቀኝነት፣ አግላይነት ዕሳቤዎችና ተግባራትን አበክሮ መታገል፣ ስኬትና ስኬታማ ዜጐችን ማድነቅ፣ ዕውቅና መስጠት፤
እራስን በትምህርት፣ በማንበብ፣ በሥልጠና በማበልጸግ እንዲሁም ከአዋቂዎች ልምድ በመገብየት ከሌሎች ጥገኝነት እና አካባቢያዊ ተፅዕኖዎች በመላቀቅ ውሳኔዎችን በምክንያታዊነት በራስ መወሰን መቻል፡፡ እንዲሁም የፈጠራ ሥራዎችን በማስፋፋት ምርታማነት እና ትርፋማነት በየዘርፉ እንዲጨምር አስተዋጽኦ ማድረግ፡፡
የሕዝብ አስተዳደርና ፖለቲካዊ ሥርዓቱ ማናቸውንም ሰው በእኩልነት የሚያይ፣ የሕግ የበላይነት የሚከበርበትና የአስተዳደርና የፖለቲካ ሥርዓት ቀረጻና ግንባታ አካታችና አሳታፊ መሆን እንደአለበት ማስተማር፣ ማስገንዘብ፣ የአስተዳደርና የፖለቲካ ችግርና ተግዳሮት ግልጽነትን ማስፈን፤ ልዩነቶች በውይይትና በምክክር መድረክና ሥርዓት ሊፈቱ እንደሚችሉ ማሳወቅ፣ ለተግባራዊነቱም አበክሮ መሥራት፤
ቀዳሚ መርሆዎችና ዕሴቶች
የእኔ ሃሣብ ብቻ ትክክል ነው” ብሎ ከማማን የራስ ወዳድነት/በላይነት (ኢጐ) ከመጠቃት ግትር፣ ትዕቢተኝነት፣ ጀብደኝነት፣ ከመሳሰሉት እኩይ ተግባራት እራስን ለማፅዳት መሥራት፣ የሚነሱ ሃሣቦችን በማሳመን፣ ወይም በማመን ይህ የማይቻል ከሆነ ጊዜው እስከሚፈታ ድረስ ላለመስማማት በማስማማት እንጂ አንጃ በመፍጠር ወይም እራስን ከስብስቡ ማግለል ነውር እና የብስለት ችግር መሆኑን መረዳት፣ ማስረዳት፤
በማናቸውም ዐውድ ውስጥ የሚከሰት ችግር ሆነ ተግዳሮት በግጭት፣ በተለይም በጦር መሣሪያ በሚከወን ትግል ሳይሆን በውይይት፣ በመነጋገር፣ በመመካከር፣ በድርድር ብቻ መፍትሔ ሊያገኝ እንደሚችል ማስገንዘብ፣ ለመፍትሔውም ሳይሰለቹ መሥራት፤
ሙስናን፣ አድሎአዊነትንና የሴቶችን መብት መጣስን መጸየፍና ለዚህ ተጠያቂ የሆኑትን ማጋለጥ፤ በሕዝብ እስከ መገለል የሚያደርስ ማህበረሰባዊ ቅጣት እንዲፈጸምባቸው የማድረግ ትግል ማካሄድ፤
8. ዜጎች በማናቸውም ዐውድ ውስጥ ያላቸውን ሀብት፣ ዕውቀትና የሥራ ልምድ ይዘው በየትኛውም የሀገሪቷ ክፍል ውስጥ በነፃነት ሊንቀሳቀሱና ሊሠሩ እንደሚችሉ፣ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ዜጎች በማንነታቸው ላይ የተመሠረተ የምቀኝነት፣ የተንኮልና ሴራ እኩይ ድርጊት ሰለባ እንዳይሆኑ ማስገንዘብ፤